በጉራጌ ዞን 27 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በጉራጌ ዞን 27 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ይለማል
ወልቂጤ ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-በጉራጌ ዞን የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ወደ 27 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ በበጋ መስኖ ግብርና ልማት ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
በክልሉ በሁለት ዙር በሚለማው የበጋ መስኖ ግብርና ልማት ስራ ያሉ የውሃ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉም እንዲሁ፡፡
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበጋ መስኖ ልማት ስራ ተጠቃሽ ነው።
በዞኑ በተያዘው የምርት ወቅት የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከ26 ሺህ 782 ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ5 ሚሊዮን 887 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው አብዛኛውን አርሶ አደር በማሳተፍ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂና የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከ120 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መቅረቡንና ስንዴን ጨምሮ አትክልትና ፍራፍሬ በበጋ መስኖ እንደሚለማ ተናግረዋል።
በመስኖ ልማቱ ከአርሶ አደሩ በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ወጣቶችም መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በአበሽጌ ወረዳ የጣውላ ቀበሌ አርሶ አደር መሃመድ ጠያር ፤ አንድ ሄክታር ማሳ በሽንኩርት ዘር ማልማት መጀመራቸውን እና የበጋ ስንዴ ለማልማት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በመቅረቡ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸው ባለፉት ስድስት ዓመታት ባከናወኑት የመስኖ ልማት ስራም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደር ዳዊት አሰፋ በበኩላቸው፤ በበጋ መስኖ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የእርሻ ስራ ውጤታማ እያደረጋቸው በመሆኑ ልማቱን በበጋ መስኖ በመድገም የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየጣሩ መሆናቸውን አንስተዋል ።
ለዚህም ከወረዳው ተገቢውን ግብዓትና የባለሙያ ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡