በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማትን በተመረጡ ወረዳዎች ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የገጠር ኮሪደር ልማትን በተመረጡ ወረዳዎች ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል
ጅማ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ግብርና ኢኒሼቲቭ፣ ቱሪዝምን እና የገጠር ኮሪደር ልማትን በተመረጡ ወረዳዎች ለመተግበር እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለፀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ''በመደመር መንግስት እይታ፣ የዘርፎች እመርታ'' በሚል መሪ ሀሳብ ለከፍተኛ አመራሮች ስልጠና በሰጡበት ወቅት ዓመቱን ሙሉ በትኩረት መሰራት ያለባቸው አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
በተለይም አንድ ግቦች ብለው ያስቀመጡት አንድ የገጠር ኮሪደር በወረዳ፣ አንድ የምርት ማከማቻ በወረዳ፣ አንድ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ማዕከል በዞን ደረጃ እና አንድ የመሶብ አገልግሎት በከተማ ይገኙበታል።
በተጨማሪም አንድ ስትራቴጂክ ኢንቨሰትመንት በክልል ደረጃ፣ አንድ አግሮ ፕሮሰሲንግ በክልል ደረጃ፣ አንድ የሽያጭ ማዕከል በከተማ ደረጃ መዘርጋት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ጅማ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን በተመረጡ ወረዳዎች ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
በዞኑ በተለይም አንድ የገጠር የኮሪደር ልማት በወረዳ፣ አንድ የምርት ማከማቻ በወረዳ እና አንድ የቱሪዝም መስህብ በወረዳ ደረጃ የማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚህም በጎማ ወረዳ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ የተጀመረ ሲሆን ይህም የገጠሩን አኗኗር ከማዘመን ባለፈ ምርታማነትን ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል።
በአጠቃላይ በዞኑ ካሉ 21 ወረዳዎች ውስጥ ስድስት ወረዳዎች የገጠር ኮሪደር እንዲሰራ የተመረጡ መሆኑን አንስተው ስራው አቅም በፈቀደ መልኩ በሁሉም ወረዳዎች ላይ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።
በወረዳው የተጀመረውን የገጠር ኮሪደር ልማት ስራ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ባሟላ መልኩ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ ይደረጋል ነው ያሉት።
በዞኑ የምግብ ዋስትናን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የተጀመረው ስራ እንደሚጠናከር ጠቅሰው ከዚህ ጎን ለጎን በወረዳ ደረጃ አንድ የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲኖር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም በሲግሞ ወረዳ የምርት ማከማቻ መጋዘን እና የምርት መሸጫ በከተማ ደረጃ የማቋቋም ስራ ለማሳካት የምርት መሸጫ ማዕከል ግንባታ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
ከዚህ በፊትም የተወሰኑ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች መኖራቸውን ተናግረው ያሉት መጋዘኖችም በቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት ለሚከናወኑ ሰብዓዊ ስራዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የተለያዩ የግብርና ኢኒሼቲቮች በመተግበር የበጋ ስንዴ እና የሩዝ ምርት፣ አቮካዶና ሙዝ እንዲሁም የማር ምርታማነት ላይ የተጀመረው ስራ በልዩ ትኩረት ይቀጥላል ብለዋል።
በተመሳሳይ በኦሞ ናዳ፣ በማናና በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳዎች የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች መኖራቸውን ገልጸው በመሰረተ ልማት አበልጽጎ በወረዳዎቹ አንድ የቱሪስት መስህብ ማዕከል እንዲኖር ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል።