ቀጥታ፡

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ዘውትር መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፡- የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ዘውትር መስራት እንዳለባቸው የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ገለጹ።

በኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ የተዘጋጀ የጥበባትና ፈጠራ ኢንዱስትሪ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።


 

የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያን ታላቅ እያደረጓት ከቀጠሉ ልጆቿ መካከል የወለደቻቸው ጠቢባን ናቸው።

መንግስት ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የልማት ስራ አስደናቂ የኪነጥበብ ስፍራዎች መገንባታቸውን ጠቁመው፤ ይህንን ላከናወኑ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር መምከራቸውንም አስታውሰዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማ በውይይቱ ነጥረው በወጡ ሀሳቦች እና በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ለመወያየት መሆኑን ተናግረዋል።

የጥበባት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ በመድረኩ ውይይት እንደሚደረግበትም ተናግረዋል።


 

እንዲሁም ከያንያን ድምጻቸውን የሚያሰሙበት የጥበባት ካውንስል ሰነድ መጠናቀቁንና በመድረኩ ውይይት እንደሚደረግበትም እንዲሁ።

በተጨማሪም የማህበራት አደረጃጀት መመሪያ ላይም ውይይት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ብዙ ገፍተው ያልሰሩበት ጉዳይ ብሔራዊ ጥቅም መሆኑን ጠቁመው፤ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅ ዘውትር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሀት፣ አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የክልሎች የባህልና ስፖርት ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም