አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር አቅም ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር አቅም ይሆናል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር አቅም እንደሚሆን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠንካራ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን በመገንባት በእውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል አዲስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉ ይታወቃል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ አዲሱ ስትራቴጂ የአረንጓዴ የክህሎት ልማት የስልጠና ፕሮግራሞችን የያዘ እና ለታዳሽ ኃይል ትኩረት የሰጠ ነው።
ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በሚደረገው ሽግግር ብቃትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስትራቴጂው ብቃት ያለው እና ለአካባቢ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን የሚተገብርና ሃብትን በቁጠባ የሚጠቀም ትውልድ ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ሥርዓተ-ትምህርቶችን በአረንጓዴ የስራ መርሆዎችና አሠራሮች በማበልጸግ ተማሪዎች ከተቋማት ሲወጡ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን እንዲጠቀሙ ያስችላል ብለዋል፡፡
አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሽግግር አቅም እንደሚሆንም ነው ሚኒስትር ዴዔታው የተናገሩት፡፡
በአዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ መሰረት የአረንጓዴ ቴክኒክና ሙያ ልጠና ፓኬጅ ተቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን አመላክተዋል፡፡፡
ይህ ፓኬጅ ከብክለትና ከብክነት የጸዳ የሃይል አጠቃቀም እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
በተቋማት ውስጥ ዘመናዊ እና ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የማሰልጠኛ መሣሪያዎችን በማስገባት ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎች በንድፈ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ልምምድ በማድረግ በሥራ ዓለም ውስጥ የአረንጓዴ ልምዶችን የመተግበር ብቃት እንዲኖራቸው እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ አዳዲስ የስራ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚያስችልም እንዲሁ፡፡