የሊጉ መሪ አርሰናል ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ አርሰናል ከዎልቭስ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ):- የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል።
ምሽት አምስት ሰዓት ላይ አርሰናል ዎልቭስን በኤምሬትስ ስታዲየም ያስተናግዳል።
አርሰናል ሊጉን በ33 ነጥብ እየመራ ሲሆን ዎልቭስ በሁለት ነጥብ የመጨረሻው 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አርሰናል በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በ10ሩ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
አርሰናል ባከናወናቸው በጨዋታዎች 28 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦች አስተናግዷል።
ተጋጣሚው ዎልቭስ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። በ13ቱ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።
ባከናወናቸው 15 ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ሲያስቆጥር 33 ግቦች ተቆጥረውበታል።
አርሰናል በ15ኛ ሳምንት በአስቶንቪላ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በፕሪሚየር ሊጉ መጥፎ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ዎልቭስ በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ለማግኘት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
አርሰናል ጨዋታውን የማሸነፍ ሰፊ ግምት ያገኘ ሲሆን ካሸነፈ ከተከታያቸው ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋሉ።
የ38 ዓመቱ ሮበርት ጆንስ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌሎች መርሃ ግብሮች ቼልሲ ከኤቨርተን እና ሊቨርፑል ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በርንሌይ ከፉልሃም ምሽት 2 ሰዓት 30 ላይ ይጫወታሉ።