በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የሚደረጉ ጨዋታዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ የሚደረጉ ጨዋታዎች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ19 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። 22 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበታል።
ሃዋሳ ከተማ በ25 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኖቹ በአሸናፊነት ጉዟቸው ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ11ኛ ሳምንት ጨዋታ የሊጉን መሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሃ ግብር አዲስ አበባ ከተማ ከመቻል ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ስምንት ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 22 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃ ይዟል።
በሊጉ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ያሸነፈው መቻል ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 18 ግቦችን በ11ዱ ጨዋታዎች ላይ ሲያስቆጥር ሰባት ግቦችን አስተናግዷል።
መቻል በ23 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ፣ መቻል ወደ መሪዎቹ መጠጋት የሚያስችለውን ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታሉ።