በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው - ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው - ተገልጋዮች
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 4/2018(ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እያገኘነው ያለው አገልግሎት ፈጣን እና እንግልትን የቀረፈ ነው ሲሉ ተገልጋዮች ገለጹ።
በማዕከሉ አገልግሎት አግኝተው ሲመለሱ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት፤ ነባሩ አገልግሎት አሰጣጥ ከአንዱ ወደ ሌላው ተቋም መመላለሱ ብሎም ቶሎ ጉዳይን ለመፈጸም አድካሚና የቅሬታ ምንጭ ነበር።
አቶ ሙፍቲ መርቀኒ ለዓመታት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማት ይመላለሱ እንደነበር አውስተው፤ ያኔ አገልግሎት አሰጣጡ ረጅም ጊዜ የሚወስድና ጉዳያቸውም ውሎ ያድር እንደነበር አስታውሰዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ ከጀመረ ወዲህ አራት ጊዜ ለአገልገሎት መምጣታቸውንና በርካታ ተቋማት በአንድ ቦታ በመኖራቸው ጉዳያቸውን በቀላሉ መፈጸም መቻላቸውን ተናግረዋል።
የንግድ ፈቃድ ለማውጣት ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ከጠበቁት በተሻለ ፍጥነት በመስተናገዳቸው በአገልግሎቱ መርካታቸውን አስታውቀዋል።
አክሲዮን ለማሻሻል፣ የንግድ ምዝገባ ለማከናወንና የንግድ መለያ ቁጥር ለማውጣት ወደ ማዕከሉ ያቀኑት ዝነኛው መዝገቡ በበኩላቸው፤ በ20 ደቂቃ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ዛሬን ጨምሮ በማዕከሉ ሁለት ጊዜ አገልግሎት ለማግኘት በማዕከሉ መገኘታቸውን ጠቁመው፤ አገልግሎት አሰጣጡ ምቹ እና ድካምን ያስቀረ ነው ብለዋል።
ጽጌ ዳኛው በበኩላቸው ማኅበር ለማጸደቅና ስያሜ ለማውጣት ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ በአምሥት ደቂቃ ውስጥ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከመጀመሩ በፊት ግን የሲስተም ችግር፣ የተቋማት በተለያየ ቦታ መሆንና የወረፋ መብዛትን ተከትሎ መስተጓጎል ያጋጥም እንደነበር አውስተዋል።
ለተለያዩ አገልግሎቶች በተደጋጋሚ ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን አንስተው፤ ከበር ጀምሮ እስከ መጨረሻ አገልግሎት አሰጣጥ ድረስ ጥሩ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ መስክረዋል።
ከጠበቅነው ጊዜ በተሻለ ፍጥነት ተስተናግደናል ያሉት ተገልጋዮቹ፤ ወጪና ጊዜን በመቆጠብ ብሎም ከአንድ ወደ ሌላ ተቋም በመመላለስ የሚከሰት እንግልትን በማስቀረት በአጭር ጊዜ አገልግሎት አግኝተናል ብለዋል።