ቀጥታ፡

ስምምነቱ ድንበር ዘለል ሽብርተኝነትንና ሌሎች ቀጣናዊ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል ከፍ ያለ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በኮንጎ ሪፐብሊክ(ብራዛቢል) መካከል የተፈረመው ስምምነት ድንበር ዘለልና ሽብርተኝነት የመሳሰሉ ቀጣናዊ ችግሮችን በጋራ ለመከላከል ከፍ ያለ ሚና እንዳለው የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ገለጹ።

በኢትዮጵያ እና በኮንጎ ሪፐብሊክ(ብራዛቢል) መካከል በወታደራዊ መስኮች ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ እና የኮንጎ ሪፐብሊክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በይፋ የተመሰረተው ኮንጎ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ መሆኑ ተመላክቷል።


 

ኢትዮጵያ በወቅቱ በአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ ውስጥ ትልቅ ሚና የነበራት በመሆኗ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ ነፃነቷን ባገኘችበት በ1960ዎቹ መጀመሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በይፋ መሥርታለች።

ግንኙነቱ በዋናነት የተጀመረው በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም በአዲስ አበባ በተመሠረተው በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) እና በአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት (AU) ማዕቀፍ ውስጥ ነበር።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው በፊርማ መርሃ ግብሩ ወቅት ገልፀዋል።

ሚኒስትሯ ከኮንጎ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር ጋር በዋናነት በወታደራዊ ኢንዱስትሪ ውጤቶች፣ በጦር መሳሪያ ጥገና፣ በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል።

ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ አቅም በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል እድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።


 

አሁን ያለንበት አለም በትብብር መስራትን ይጠይቃል ያሉት ኢንጂነር አይሻ ድንበር ዘለልና ሽብርተኝነት የመሳሰሉ ቀጣናዊ ችግሮችን በጋራ ለመከላከልም ከፍ ያለ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖረን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።

የኮንጎ ብራዛቢል መከላከያ ሚኒስትር ቻርለስ ሪቻርድ ሞንጆ በበኩላቸው ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ሰላምና ደህንነት የበለጠ ለማጎልበት የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመቀየር በቅርቡ ወደ ተጨባጭ ስራ እንገባለን ነው ያሉት።

ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ኮንጎ ብራዛቢልን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም