የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደግፍ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደግፍ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር የቢዝነስ ፎረም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደግፍና የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ገለጹ፡፡
የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር በበኩሉ፤ በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛ ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ አገሮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዳዋኖ ከድር፣ በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጂንግ ካንግ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ እንዳሉት፤ ኮሪያ ሪፐብሊክ በአምራች፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በአይ ሲ ቲ፣ በዲጂታል ሥርዓትና በኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር ናት፡፡
የኮሪያ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግንባታ፣ በኢንጂነሪንግና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሰማራት ጥራታቸውን የጠበቁ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ፎረሙ የኢትዮጵያና ኮሪያ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የበለጠ የሚያጠናክር ከመሆኑም ባለፈ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደግፍና የሥራ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና ኮርያ መካከል ጠንካራ ወዳጅነት አለ።
የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ የሥራ ተቋራጮች ማህበር በግንባታ፣ በአረንጓዴ ቴክኖሎጂ፣ በፕሮጀክት ማኔጅመንትና በኢንጂነሪንግ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ማህበሩ በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ባሉት የመሠረተ ልማት እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም እንዲሁ፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛ ምስራቅ፣ ኤዥያና ፓስፊክ ሀገራት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዳዋኖ ከድር እንደገለጹት፤ የኮሪያ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰማራቱ ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡
የኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዝዳንት ሃክ ሶ ዮን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ማህበሩ ለሁለቱ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ትብብር መጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በስር ያሉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ዘርፍ መሰማራት እንደሚፈልጉም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።