የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን ጠብቆ መታደሱ የአካባቢውን ታሪክ የተሟላ ያደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን ጠብቆ መታደሱ የአካባቢውን ታሪክ የተሟላ ያደርገዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ የአካባቢውን ታሪክ የተሟላ እንደሚያደርገው ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የሚገኘውን እና 129 ዓመታትን ያስቆጠረውን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተክርስቲያን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ ቤተ ክርስቲያኑ ከዓድዋ ድል ታሪክ ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ነው። በፋሽስት ወረራ ጊዜ በእሳት መቃጠልና ጥቁር ቀለም እስከ መቀባት ዋጋ ከፍሏል ብለዋል።
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን በጠበቀና ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየታደሰ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የህንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የጥበበ ዕድና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ አስደናቂ መሆናቸውን አድንቀዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ፣ የዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ጥገና እና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ አድርጎታል ነው ያሉት።
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ ደግሞ የአካባቢውን ታሪክ የተሟላ እንደሚያደርገው አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ የቤተ ክርስቲያኑን እድሳት ሥራው ከከተማዋ የቱሪዝም ልማትና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር እንዲጣጣም ሁሉም አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ገነት ክብሩ ገብረጻድቅ፤ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ከቀለም ቅብና ጥቃቅን ጥገናዎች ያለፈ እድሳት እንዳልተደረገለት ጠቅሰዋል።
ሆኖም ከዕድሜው ብዛትና በተለያዩ ምክንያቶች በጉልላቱ፣ በእሳት መከላከያ ጣሪያው እና በዙሪያው ጉዳቶች በመከሰታቸው የባለሙያዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተሟላ ዕድሳት መገባቱን ገልጸዋል።
የዕድሳት ሥራው በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ አክለውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የቤተ ክርስቲያን እድሳት ሥራውን በአካል ተገኝተው በመመልከታቸው ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
ጉብኝታቸው ቤተ ክርስቲያኑ የሀገር ታሪክና ቅርስ በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ መንግሥት የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የቅርስ ሥራዎች ከፍተኛ የኪነ ህንጻ ባለሙያ አርክቴክት ኤፍሬም ንጉሤ እንዳሉት፤ እድሳቱ ከመጀመሩ በፊት ለስድስት ወራት ዝርዝር ጥናት ተደርጓል።
በጥናቱ ቤተ ክርስቲያኑ በታሪኩ ከቀለም ቅብና መሰል ቀላል ሥራዎች ያለፈ ዋና ጥገና ተደርጎለት እንደማያውቅ ተረጋግጧል ነው ያሉት።
ጉልላቱ፣ በዓይነቱ ልዩ የሆነው የቤተ ክርስቲያኑ እሳተ ከላ እና ሌሎችም ክፍሎች በእርጅና ምክንያት ዝናብ እስከማስገባት ስለደረሱ ወደ ስር ነቀል ጥገና መገባቱን ገልጸዋል።
የቅድሳት ሥዕላቱን የማደስ፣ የመስታወት ጌጦችን በነበሩበት ይዞታ የማስተካከል እና ሌሎች የእጅ ጥበብ የሚሹ ውድ ሥራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ቤተ ክርስቲያኑ መጀመሪያ ሲሰራበት የነበረውን ድንጋይ፣ አሸዋ፣ ኖራ እና ሲሚንቶ ያለመቀየር መርህን በመከተል በከፍተኛ ሙያዊ ጥንቃቄ እየታደሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
መምህር ግሩም ጌታቸው የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ የህንጻ እድሳት አሰባሳቢ ዐቢይ ኮሚቴ የገቢና ቅስቀሳ ክፍል ሰብሳቢ ናቸው።
የእድሳት ሥራው አጠቃላይ 157 ሚሊዮን ብር የሚወስድ ሲሆን፤ በሕዝብ ድጋፍ እየታደሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ቅርስና ሀብት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የዕድሣት ሥራው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።