ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጧ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 32ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት(ኮፕ-32) ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል የዲፕሎማሲ አመራር የተገኘ ስኬት መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ /ኮፕ-32/ በተመለከተ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በአራዳ ፓርክ ተካሂዷል።


 

በመርሀ ግብሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሀይ ጳውሎስ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፣ የመዲናዋ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተለያዩ ባለሃብቶች እንዲሁም አልሚዎች ተገኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሳል የዲፕሎማሲ አመራር የተገኘ ስኬት ነው።

ይህም ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑን ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር፣ በከተሞች ልማትና ውበት የተመዘገቡ ውጤቶች ዓለም አቀፉን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሎም አዲስ አበባ የዓለም የስበት ማዕከል መሆናቸውን በመጥቀስ፣ መዲናዋ ባለፈው ዓመት በርካታ ዓለም አቀፍ፣ አሕጉራዊ እና ሀገራዊ ሁነቶችን ማስተናገድ መቻሏን ገልጸዋል።

ኮፕ-32 የዓለማችን ትልቁ የትኩረት ማዕከል መሆኑንም ነው የተናገሩት።


 

ጉባኤው ለኢትዮጵያውያን ብዙ ዕድል ይዞ ይመጣል ያሉት ከንቲባዋ፤ ለዚህ ደግሞ መንግሥት የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማዘጋጀት ዕድል እንድታገኝ፣ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለማሳየትና የስራ ዕድል ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ባለሀብቶች አልሚዎችና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር በመተባበር ጉባኤውን በስኬት ለማካሄድ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ጉባኤውን በብቃት በማስተናገድ ለኢትዮጵያ ለውጥ መሰረት መጣል አለብን ያሉት ከንቲባዋ፤ ዛሬ የስራ ክፍፍል በማድረግና ዝግጅት በመጀመር ግባችንን ማሳካት አለብን ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምጸሀይ ጳውሎስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ኮንፍረንሶችን በብቃት ማስተናገድ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸው፤ ውጤቱም በጋራ ትብብር የተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ለቀጣይ ስራዎቻችን መስፈንጠሪያ እንደሚሆኑ በመጥቀስ፤ ኮፕ-32 እንዲሁ የተገኘ አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤ አዘጋጅነትን ለማግኘት ዓለም አቀፋዊ ውድድር ማድረግ ነበረባት ያሉት ኃላፊዋ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌሎችም አረንጓዴ ልማት ስራዎች በተገኙ ውጤቶች መመረጧን በመግለጽ።

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ወራት ከ105 በላይ ሁነቶችን ማዘጋጀቷን ገልጸው፤ እነዚህ ስኬቶች የኮፕ 32 ጉባኤ ዝግጅትን በድል እንደምንወጣ የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።

በብራዚል ቤለም በተካሄደው 30ኛው ጉባኤ ላይ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን 32ኛ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ(COP-32) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም