ቀጥታ፡

ሰላምን በማስጠበቅ የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ስልጠናው የተሻለ አቅም ፈጥሮልናል - አመራሮች

ገንዳ ውኃ፣ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ):- በመደመር መንግስት ዕይታና እሳቤዎች  ላይ  የተሰጣቸው ስልጠና ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን ተረድተው  ሰላምን በማስጠበቅ የሕዝብን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተሻለ አቅም እንደፈጠረላቸው  በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰልጣኝ አመራሮች ገለጹ። 

በገንዳ ውኃ ከተማ ለዞኑ ለመካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል። 

የስልጠናው ተሳታፊ ኑርሁሴን ሙሃመድ ፤ በስልጠናው የመደመርን መንግስት ዕይታ በመረዳት የተሻለ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም  እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። 

መዋቅራዊ ሽግግር፣ ኢንዱስትሪ ልማት፣ ከተማ ልማት እና ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ የተሰጣቸው ስልጠና  በቂ እውቀት ያስጨበጠ ነው ብለዋል። 

ስልጠናው ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን መረዳት እንዲችሉ ማድረጉን ጠቅሰው፤ በዚህም ቀጣይ ሁሉን አቀፍ የሰላም ግንባታና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ልማቶችን በቁጭትና በተነሳሽነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

ሌላው ተሳታፊ አቶ ሀብቴ አዲሱ፤  የከተማ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግና ሆቴል ቱሪዝም ያልተሰራበትና በርካታ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከስልጠናው የተገኘውን አቅም ወደ መሬት በማውረድ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ልማቶችን በቁጭት ለማከናወን የተሻለ አቅም ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው እያንዳንዱ ዘርፍ የሚፈልገውን እውቀትና ክህሎት ያገኘንበት በመሆኑ ለቀጣይ ስራችን አቅም ፈጥሮልናል ያሉት ደግሞ ሌላኛው ሰልጣኝ ፍሬ ህይወት ምስጋናው ናቸው። 

በስልጠናው ባገኙት እውቀት ሕዝብን ያሳተፈ የሰላም ግንባታና ልማትን ለማጠናከር ካለፉት ጊዜያት በተለየ ክትትልና ቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ እያሱ ይላቅ በበኩላቸው፤ ስልጠናው የአመራሩን የመምራትና የማደራጀት አቅም ከፍ ያደረገና ትልቅ ተነሳሽነትና ቁጭት የፈጠረ ነው ብለዋል።

በተለይም እንደ ሃገር የተቀመጡ ኢኒሸቲቮችን በትክክል ለመተግበርና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ስልጠናው አቅም ፈጥሯል ሲሉ አብራርተዋል። 

በተለይም የከተማ ትራንስፎርሜሽን፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የገጠር ኮሪደር፣ ቱሪዝም ልማትና ኢንዱስትሪ ማስፋፋት የአመራሩ ልዩ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። 

በስልጠናው በየደረጃው የሚገኙ መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም