ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጎንደር ከተማ ማሳያ ናት - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጎንደር ከተማ ማሳያ መሆኗን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

በጎንደር ከተማ በአምራች ኢንዱስትሪና በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡ ውጤቶች የበርካታ ዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በጎንደር ከተማ በሌማት ትሩፋት፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፎች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፥ በጎንደር ከተማ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያላቸው የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በጎንደር ከተማ በሁሉም መስክ የሚታየው ትርጉም ያለው የልማት እንቅስቃሴ የከተማዋን ለውጥ ከማፋጠን ባለፈ በርካታ ዜጎችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተሰማሩ ማኅበራትና ኢንተርፕራይዞችም የምግብ ዋስትናን እያረጋገጡ መሆናቸውን አንስተዋል።

የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለሀገር በቀል የክህሎት ልማት ትኩረት መስጠቱ ብቁ የሰው ኃይልን በማፍራት የኢንዱስትሪ ሽግግርን እያሳለጠ ወጣቶችንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስኬቶች በሁሉም ዘርፍ እየተመዘገቡ መሆኑን ጎንደር ከተማ ማሳያ መሆኗንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በጎንደር በአመራር ትጋት በአጭር ጊዜ የተመዘገቡ ለውጦች ታሪካዊቷን ከተማ እንደገና በመውለድ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር በጎንደር ከተማ ለሚከናወኑ የክህሎት ልማትና ስልጠና ተግባራት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።


 

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፥ በከተማዋ በኢንዱስትሪና በሌማት ትሩፋት የተመዘገቡ የልማት ውጤቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዶሮ እርባታ፣ በእንቁላል፣ ወተትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት የተገኙ ውጤቶች በቂ ምርት ለገበያ በማቅረብ ፍላጎትን በማሟላት ረገድ ሚናቸው የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም