ቀጥታ፡

በክልሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ሊጠናከር እንደሚገባ ተመላከተ።

"ጥቃትን የማይታገስ ማህሕበረሰብ ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የተዘጋጀ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ፤ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የሁላችንንም ርብርብና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

ልማትም ሆነ ብልፅግና ለማረጋገጥ የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን በመጠበቅ ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የሚደረገውን ሂደት ለማጠናከርም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቆም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ፆታዊ ጥቃትንና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በተደረገው ጥረት አበረታች ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል።

ችግሩን ከመከላከል ጎን ለጎን በክልሉ 17 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የስነ-ልቦና ምክር፣ የጤናና የሕግ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ፍትህ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባልም ነው ያሉት።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን ማስቀጠል ይኖርብናል ያሉት ደግሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም ናቸው።

ፆታዊ ጥቃት ፈፅመው በተገኙ 289 ግለሰቦች ላይ ከ3 እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

ከአንድ ሺህ 400 ለሚበልጡ ሴቶች ደግሞ ነፃ የሕግ አገልግሎት ድጋፍ መስጠት መቻሉን ጠቅሰው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልና ለማስቆም ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናከሮ ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም