በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት እየተመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት እየተመዘገበ ነው
ቦንጋ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሌማት ትሩፋት መርሀግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በመደመር መንግስት እይታ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸውና ባለሁለት አሀዝ እድገት ለማስመዝገብ ግብ ከተጣለባቸው መካከል የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ተጠቃሽ ነው።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ታመነ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በተለያዩ ዘርፎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡
መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ በወተት፣ በማር፣ በዶሮ፣ በሥጋና በዓሣ 2ሺህ 650 መንደሮች መደራጀታቸውን ገልጸው፣ በዚህም በየዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ከመቀየር ባለፈ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብልዋል።
እንደ አቶ ታመነ ገለጻ በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከመጀመሩ በፊት ዓመታዊ የማር ምርት 56 ሺህ 275 ቶን ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት ይህ ቁጥር ወደ 71 ሺህ ቶን ከፍ ብሏል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ምርቱን 80 ሺህ ቶን ለማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ሲሆን ባለፉት አምስት ወራትም 15 ሺህ ቶን ማር ለማምረት መቻሉን ጠቁመዋል።
የዓሣ መንደሮችን ለማደራጀት በተከናወኑ ተግባራትም ለውጥ መመዝገቡን የጠቀሱት አቶ ታመነ በበጀት ዓመቱ 9 ሺህ ቶን ዓሣ ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የሺሾ-እንዴ ወረዳ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አዱኛ አለሙ በበኩላቸው እንዳሉት የአካባቢውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በወረዳው 233 የማር፣ የወተት፣ የዓሣና የዶሮ መንደሮች ተደራጅተዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም በተበታተነና በባህላዊ መንገድ ሲያከናውን የነበረውን ሥራ በማዘመን ተጠቃሚ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡
በወረዳው በዋናቦላ ቀበሌ በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደር አክሊሉ ወልደሚካኤል እና ታምራት ተክሌ በተደረገላቸው የባለሙያና የግብዓት ድጋፍ ውጤታማ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት እያንዳንዳቸው ሀምሳ ዘመናዊና ባህላዊ ቀፎዎች እንዳላቸው የተናገሩት አርሶ አደሮቹ ከአንዱ ቀፎ ከ35 እስከ 40 ኪሎ ግራም ማር እንደሚያገኙ ተናግረዋል።
ሁለት የዓሣ ገንዳዎችን በማዘጋጀት በዓሣ እርባታ ሥራ የተሰማሩት አርሶ አደር ደምሴ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የአሣ ምርታቸውን ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ከዚህ ቀደም በአካባቢው ያልተለመደውን የዓሣ እርባታ ሥራ በማስጀመር ለህብረተሰቡ የገቢና የምግብ አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።