ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ በአንጎላ ሉዋንዳ እየተካሄደ የሚገኘው አራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።
የሴቶች ብስክሌት የግል ሰዓት ሙከራ ውድድር ማህደር ደስታ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ከሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ወጣቶች ጨዋታዎች የተገኘችው ማህደር ያገኘችው ወርቅ በውድድሩ ለኢትዮጵያ ሶስተኛ የወርቅ ሜዳሊያ ሆኖ መመዝገቡን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ በ3000 ሜትር ሴቶች እና በሴቶች ብስክሌት የቡድን የሰዓት ሙከራ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች በሰባት የስፖርት አይነቶች 70 ስፖርተኞችን እያሳተፈች ይገኛል።
አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ክብደት ማንሳት ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።
በአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ስፖርተኞች በቅርቡ በተካሄደው ሁለተኛው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ ባስመዘገቡት ውጤት የተመረጡ መሆናቸው ይታወቃል።
በውድድሩ ላይ 54 ሀገራት በ33 የስፖርት አይነቶች እየተሳተፉ ነው። አህጉራዊው የስፖርት ሁነት እስከ ታህሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታዎች በ2019 ዓ.ም በሴኔጋል ዳካር ለሚካሄደው አራተኛው የወጣቶች የክረምት ኦሊምፒክ እንደ ማጣሪያ እና መዘጋጃ የሚያገለገል ውድድር ነው።