ወንጀልን በመከላከልና ሰላም በማስጠበቅ የፖሊስና ሕብረተሰቡ ትብብር ጎልብቶ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ወንጀልን በመከላከልና ሰላም በማስጠበቅ የፖሊስና ሕብረተሰቡ ትብብር ጎልብቶ ሊቀጥል ይገባል
ደብረ ብርሃን፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፡- ወንጀልን በመከላከልና የሰላም በማስጠበቅ ስራ የፖሊስና ሕብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር ጎልብቶ ሊቀጥል እንደሚገባ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
በደብረ ብርሃን ከተማ በወንጀል መከላከል እና በዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የስልጠና እና ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ዓባይ ሙሉጌታ፤ ለወንጀል መከላከልና የሰላም ማስጠበቅ ስራ የፖሊስና ሕብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በደብረ ብርሃንና አካባቢው ያለውን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ የልማትና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።
በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በሚንቀሳቀሰው የሽፍታው ስብሰብ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አንስተው፤ ለሰላም አማራጭ ዝግጁ የሆኑትንም አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሰላም ግንባታ የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ብቃትና ቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አባይ ኢሌ፤ በዞኑ የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎች በየዕለቱ እየገቡና አቀባበልም እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በዞኑ ያለው ሰላምና መረጋጋት በአስተማማኝ መልኩ መቀጠሉን አንስተው፤ የጸጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር የሰላም ግንባታ ስራው ይቀጥላል ብለዋል።