የክትባት ሽፋንን በማሳደግ ፖሊዮን ለማጥፋት ትኩረት ተደርጓል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የክትባት ሽፋንን በማሳደግ ፖሊዮን ለማጥፋት ትኩረት ተደርጓል - ጤና ሚኒስቴር
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፡-የክትባት ሽፋንን በማሳደግ ፖሊዮን ከሀገር የማጥፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ሀገር አቀፍ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል ፡፡
የጤና ሚኒስትሯ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2017 “ዋይልድ” የተሰኘውን የፖሊዮ ቫይረስ ማጥፋት መቻሏን ገልፀዋል።
በድንበር አካባቢ ያለውን የፖሊዮ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከአምና ጀምሮ እንደ ሀገር የክትባት ሽፋንን በማሳደግ ፖሊዮን ከሀገር የማጥፋት ሥራ በዘመቻ መልክ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አምና በመጀመሪያው ዙር 15 ሚሊዮን እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 16 ሚሊዮን የሚሆኑና ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን መከተብ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ዘንድሮም በመጀመሪያ ዙር በሰባት ክልሎች ላይ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ክትባቱን ማዳረስ እንደተቻለ ገልፀው በአሁኑ ዘመቻም ሽፋኑን በማሳደግ 24 ነጥብ 8 ሚሊዮን ህፃናትን ለመከተብ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህንን ስኬታማ ለማድረግም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ የክትባት ዘመቻው ቤት ለቤት የሚካሄድ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ከፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ጎን ለጎንም የማርበርግ ቫይረስ በሽታን የመከላከልና የቁጥጥር ተግባርን ለማጠናከር የቤት ለቤት ቅኝት እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡
ፖሊዮን ማጥፋት መጪው ትውልድ ጤናማ እና ምርታማ እንዲሆን መስራት ነው ያሉት ደግሞ በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ ናቸው፡፡
በክልሉ ፖሊዮን ጨምሮ በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ በሽታዎችን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ በበኩላቸው ለዘመቻው ስኬት በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ለማህበረሰቡም በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራቱን የተናገሩት ኃላፊዋ ህብረተሰቡ ቤት ለቤት በሚደረገው የክትባት ዘመቻ ለጤና ባለሙያዎች ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አመራሮች የተገኙ ሲሆን ወላጆችም ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡም መልዕክት ተላልፏል።