ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዕድገት የድርሻውን እንደሚወጣ ተስፋ የተጣለበት የካካዋ ምርት

በኢትዮጵያ የካካዋ ምርትን በማላመድና በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ለካካዋ ምርት ተስማሚ ሥነ-ምህዳር እንዳላት በጥናት ተረጋግጦ ወደ ተግባር መገባቱንም ነው ኢንስቲትዩቱ ያመለከተው።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ካካዋ በዓለማችን በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ የኢንዱስትሪ ግብዓት ተክሎች መካከል አንዱ ነው።

ምርቱ ቀደም ሲል በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በብዛት ይመረት እንደነበር አስታውሰው ምርቱን በኢትዮጵያ ለማላመድ በርካት የጥናትና ምርምር ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ካካዋን በኢትዮጵያ ለማላመድና ለማምረት የተከናወኑ ስኬታማ የጥናትና ምርምር ስራዎች የንብ ቸኮሌትን በሀገር ውስጥ ማምረት ያስቻለ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱንም ነው የገለጹት።

ምርቱ የወጪ ንግድን በማሳለጥ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ዕድገት የድርሻውን እንደሚወጣ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን የካካዋ ምርታማነት ለማሳደግም ለግልና የመንግስት የካካዋ አምራቾች ችግኞችን በማዘጋጀት የማባዛት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አልሚ ባለሃብቶችም የካካዋ ምርታማነትን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ነው የመከሩት።

ኢንስቲትዩቱ የካካዋ ችግኞችን በከፍተኛ መጠን በማዘጋጀት የካካዋ ምርትን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማግኘት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይም የሰብል ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ዝርያዎችን የምርታማነት አቅምን የሚያሳድግ ጥናት በማከናወን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የብሔራዊ ቅመማቅመም አስተባባሪ እና ተመራማሪ አቡኪያ ጌቱ በበኩላቸው፤ የካካዋ ምርት በስፋት ለማምረት በአሁኑ ሰዓት በርካታ የካካዋ ችግኞች የማባዛት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም