በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ ይኖረዋል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ ይኖረዋል -የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በሰሜን፣ ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ደጋማ የአገሪቱ ክፍሎች የሌሌቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንደሚስተዋል አስታውቋል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት በመነሳት ወደ አገራችን የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ቅዝቃዜው ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየሽ በታች እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስታውቋል።
በዚህም በሰሜን ፣ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ደጋማ የአገሪቱ ክፍሎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ አንጻራዊ ጥንካሬ እንደሚኖረው ገልጿል።
አልፎ አልፎ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ውርጭ የማስከተል ጥንካሬ እንደሚኖረውም ጠቁሟል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ጥቂት ቦታዎች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ብሏል።
በተጨማሪም በሰሜን ምዕራብ፣ ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች አልፎ አልፎ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ገልጿል።
በዚሁ ወቅት አብዛኛው ተፋሰሶች ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።