ቀጥታ፡

አገልግሎቱ አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረጉ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረጉ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቶፊክ ሻፊ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት አገልግሎቱ አሰራሩን ዲጂታላይዝ በማድረጉ ደንበኞች ቀልጣፋና አስተማማኝ መስተንግዶ እያገኙ ነው።

አገልግሎቱ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የቴክኖሎጂ ትስስር መፍጠር በመቻሉና የፋይዳ መታወቂያን በአስገዳጅነት በመጠቀሙ ችግሩን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

የመረጃ ቋት ስርዓት በመዘርጋት ሀገራዊ ሰነድ የማረጋገጥና የመመዝገብ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማጠናከርና ተደራሽነትን በማስፋት ተገልጋዮች ያለ ወረፋ እንዲስተናገዱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል።

በዚህም አገልግሎቱ ባሉት ቅርንጫፎች ለተገልጋዮች ፍላጎት ፈጣን ምላሽ በመስጠት ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በአጠቃላይ ከወረቀት ወደ ዲጂታላይዜሽን የሚያደርገው ሽግግር በተሳካ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች እንዲሳለጡና የማህበራዊ መስተጋብር ጤናማነት እንዲረጋገጥ አገልግሎቱ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተገልጋዮች በበኩላቸው በተቋሙ ባገኙት አገልገሎት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ከበደ ወልደጊዮርጊስ እንዳሉት ተቋሙ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየሰጠ ባለው ቀልጣፋ አገልግሎት በመታገዝ በአጭር ጊዜ ጉዳያቸውን አጠናቀው መመለስ ችለዋል።

በተቋሙ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከዚህ በፊት ከነበረው አንጻር መሻሻሉንም ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ዘሃራ መሀመድ በበኩላቸው ባገኙት አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸው የሚሰጠው አገልግሎት ከነበረው በእጅጉ መሻሻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በምቹ የአገልግሎት መስጫ ቦታ በአጠረ ጊዜ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ነው የጠቆሙት።

የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና ቀልጣፋ በመሆኑ ጥሩ አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ አንዋር አህመድ ናቸው።

ቀደም ሲል ከወረፋ ጋር በተያያዘ ይታዩ የነበሩ ችግሮች አሁን ላይ መቀረፋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም