በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ሰላምን ዘላቂ በማድረግ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማጠናከር ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በወቅቱ እንዳሉት የክልሉን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ማጠናከር ይገባል።
በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የሰላም ግንባታና የልማት ስራዎችን ወደኋላ ለመመለስ እኩይ ዓላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የፀረ-ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ በመግታት የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል።
በዚህ ረገድ በህዝብና በፀጥታ መዋቅሩ እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም የክልሉን ሰላም በማጽናትና የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል ረገድ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው በአመራሩ ዘንድ ያለውን የሃሳብና የተግባር አንድነት በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንተጋ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በቅርቡ ለአመራሩ የተሰጠውን የአቅም ግንባታ ስልጠና በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገትና ዘላቂ ሰላም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሰላምን ለማደፍረስና ልማቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሀይሎችን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ የተጀመሩ ጥረቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሺኔ አስቲን በበኩላቸው አመራሩ የጋራ የሆኑ ትርክቶችን መገንባት ከቻለ የማይፈቱ ችግሮች አይኖሩም ብለዋል።
በመሆኑም አመራሩ አንድነቱን በማጠናከር የፀረ ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ በጋራ መግታት እንደሚገባ አመላክተዋል።