ቀጥታ፡

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎትን በማዘመን ህብረተሰቡ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው

አሶሳ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎትን በማዘመን ህብረተሰቡ ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑን የፌዴራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ኪኒሶ ተናገሩ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባን በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።


 

በዕለቱ የተገኙት የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ኪኒሶ እንደተናገሩት፤ ዜጎች በሁሉም ዘርፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት እየተሰራ ነው።

የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት በርካታ ተገልጋዮችን የሚያስተናግድ በመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀረሪ፣ ሲዳማና አማራ ክልሎች ዲጂታል የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት እያከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ ዲጂታል መሆኑ ተዓማኒነት ያለው አሰራርን ከመፍጠር ባለፈ የመረጃ ደህንነትን በመጠበቅ አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና የክልሉ ፍትህ ትራንስፎርሜሽን ሰብሳቢ ወይዘሮ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፤ አገልግሎቱ የዜጎችን እንግልት የሚያስቀር እና በተገልጋዩና በመንግስት ተቋማት መካከል ያለውን መተማመን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ተቋማት በራሳቸው አቅም አሰራራቸውን በማዘመን የዲጂታል አገልግሎት እንዲስፋፋ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎትም በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ በቢሮው የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚቀርፍ ነው ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሐመድ ሀሚድ ናቸው።


 

በቀጣይም የዲጂታል አሰራሩን እስከታችኛው መዋቅር በማውረድ ዘርፉን የማዘመን እና አገልግሎት አሰጣጡን የተሳለጠ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም