የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማሳካት ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ትልቅ እድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማሳካት ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ትልቅ እድል ነው
ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማሳካት ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ትልቅ እድል መሆኑ ተመላከተ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን በሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል የዲፕሎማሲ መርህ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መነሻነት ለመጨረስ እየሰራች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በዚህ ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ከ120 ሚሊየን በላይ የህዝብ ብዛት ያላት ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ-ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሆኑን ማስገንዘባቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት በሴራ ያጣችውን የባሕር በር ምላሽ ለማስገኘት የሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ድሬዳዋ ካምፓስ መምህራን የባህር በር ባለቤት የመሆን ጉዳይ ትናንት፣ ዛሬንና ነገን ያስተሳሰረ የትውልድ ጥያቄ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር ግርማ አክሊሉ፣ ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ፣ በርካታ ህዝብ ያላትና ከባህር በር በቅርብ ርቀት የምትገኝ ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል።
የባህር በር ባለቤትነቷን ያጣችበት መንገድም በሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጥ ቁጭት የፈጠረ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ የቀጠለ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ወቅትም አጀንዳ መሆኑ ተገቢ እና ትክክለኛ ነው ብለዋል።
ይሄን የትናንት፣ የዛሬና የመጪው ትውልድ ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህግና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍትሄ እንዲሰጠው ወደ ዓለም አደባባይ መውጣቱ ትልቅ እርምጃ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባል ነው ያሉት።
በተለይም እየተመዘገበ የሚገኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዞን ለማስቀጠል የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄን ማሳካት የህልውና መሠረት መሆኑን አስረድተዋል።
ምሁራንም ይሄን የትውልድ ጥያቄ በማስተጋባትና በማስረዳት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ መመህሩ ሰለሞን ሰቦቃ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን እየተገበረች ያለችው የብዝሃ ኢኮኖሚ እና ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተጨባጭ የሚፈለገውን ውጤት በማስመዝገብ የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ የባህር በር ባለቤትነት ሲሳካ ነው ብለዋል።
የባህር በር ባለቤት የመሆን ጉዳይ የኢትዮጵያን አለም አቀፍ ዕድገት፣ ደህንነትና ተቀባይነት በላቀ ደረጃ የሚያሳድግ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ጥያቄዎች በተሟላ መንገድ መመለስ የሚያስችል መሆኑን አስምረውበታል።
የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ መሳካት ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ትልቅ እድል መሆኑንና ለተፈጻሚነቱ በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።