ዘላቂ የሰላም ስምምነቱ የፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ለህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ የሰላም ስምምነቱ የፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ለህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ መስራት ይገባል
ጎንደር ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ዘላቂ የሰላም ስምምነቱ የፈጠረውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም አመራሩ ለህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት ይበልጥ መስራት እንደሚገባው ተመላከተ።
"በመደመር መንግስት እይታ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሃሳብ በጎንደር ከተማ ለመካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ መንግስትና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋሃድ) መካከል በቅርቡ የተደረገው ዘላቂ የሰላም ስምምነት መንግስት ችግሮች በውይይትና በንግግር እንዲፈቱ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ትልቅ እርምጃ ነው።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በዞኑ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መርጠው ሰሞኑን መመለሳቸውን ጠቁመው፣ ይህም ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም አመራሩ በስልጠና ባገኘው እውቀትና ግንዛቤ ታግዞ የመደመር መንግስት እሳቤዎችን ወደ ተግባር በማሸጋገር ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት በትጋት መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ግብርና፣ ቱሪዝም፣ የከተማ ልማት ሥራ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዘርፍ ስልጠናው በዋናነት ያተኮረባቸው አቅጣጫዎች እንደሆኑ ጠቁመው፣ አመራሩ እነዚህን ዋነኛ የልማት ውጥኖች ለማሳካት በጊዜ የለኝም መንፈስ እንዲሰራ አሳስበዋል፡፡
ገቢ አሰባሰብ፣ ከተማ ግብርና፣ ትምህርት፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ ህገ ወጥ ንግድ ቁጥጥርና ገበያ ማረጋጋት ስራዎች የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ሊሆኑ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የዞኑ ሰላም ጸንቶ እንዲቀጥል ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመረውን ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስተዳዳሪው አንስተዋል።
ስልጠናው በአመራሩ መካከል የሀሳብና የተግባር አንድነት እንዲኖር በማድረግ በኩል ትልቅ አቅም ሆኖናል ያሉት ደግሞ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የስልጠናው ተሳታፊ አቶ መንግስቱ ቻላቸው ናቸው፡፡
የመደመር መንግስት እሳቤ ሀገር የማሻገር ትልቅ ርዕይ የሰነቀ ሀገር በቀል እውቀት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አመራሮች በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳደር የመጡት ወይዘሮ ሰላማዊት መሳፍንት በበኩላቸው፤ በዞኑ ተስፋ ሰጪ የሰላም ሁኔታ በመፈጠሩ ለህዝቡ የልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።
ስልጠናው ሀገራዊና ክልላዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ በቀጣይ አመራሩ ሊያከናውናቸው የሚገቡ የተግባራት አቅጣጫዎችን ያመላከተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።