ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎብኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ እንብርት የሚገኘውን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያኑ ከዓድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ታሪክ እንዳለው እና በዚህም የተነሣ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ጊዜ እንደ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ ዋጋ መክፈሉን አውስተዋል።
በእሳት እስከ መቃጠልና ጥቁር ቀለም እስከ መቀባትም ደርሶ እንደነበርም አመልክተዋል።
ቤተ ክርስቲያኑ ደረጃውን በጠበቀና ልዩ ልዩ ባለሞያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየታደሰ መሆኑን በጉብኝታቸው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የዓድዋ ሙዝየም በአካባቢው መገንባቱ፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ዐደባባይ ጥገና መደረጉ እና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ አድርጎታል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከል እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል።
አሁን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያን ሕንጻና ግቢ ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ ታሪኩን የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል ነው ያሉት።
የሕንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የጥበበ ዕድ እና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ አስደናቂ ናቸው ብለዋል።
የቤተ ክርስቲያኑ እና የአካባቢው ጥገና አሁን ከጀመርናቸው የከተማ ማዘመን ሥራዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።