ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ ይኖርባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ ይኖርባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ለምክክርና ንግግር ራሳቸውን በማዘጋጀት በሀገራዊ ምክክሩ መሳተፍ እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና አካታች ምክክር በማድረግ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ኮሚሽኑ ከተመሰረተበት ዓላማ መካከልም ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ክልላዊም ሆነ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማካሔድ በታሰበው ሃገራዊ ምክክር ላይ ተሳትፎ በማድረግ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ችግሮች ለመፍታት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር እየሰራ ሲሆን፤ በአብዛኛው በሚባል ደረጃ በስሩ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አጀንዳ በመሰብሰብ ለኮሚሽኑ ማስረከቡን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከመነሻው ጀምሮ በምክክር ሂደቱ ያልተሳተፉና ከተሳተፉ በኋላም ያቆሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግም ውይይቶችና ኮንፈረንስ እየተደረገ መግባባት ላይም እየተደረሰ መሆኑን ገልፀዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎችም በተጨማሪ ጫካ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ወደ ምክክሩ በመምጣት ቀጣዩን ትውልድ የሚጠቅሙ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅባቸው ነው የተናገሩት።
እንደ ሀገር የሚነሱትን ችግሮች ለመፍታት ከምክክር ውጭ አማራጭ የለም የሚሉት ዋና ሰብሳቢው፤ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው ብለዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ባሻገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ ውስጥ በመሳተፍ ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ማበርከት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ኢትየጵያ ብዝሃ ሀገር ነች ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በመደማመጥና በሀሳብ የበላይነት በመመራት የሀገርን ሰላም ማጽናትና የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓትን የመገንባት ስራ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አለመሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢው፤ በየደረጃው ርብርብ በማድረግ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገሪቷ ያሉትን ችግሮች ከመፍታት አኳያ ትልቅ እፎይታን የሚሰጥና ችግሮችን የሚያቃልል መሆኑንም ነው ያነሱት።
በቅርቡም በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩ ወገኖች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ለማህበረሰቡና ለሀገር ሰላም በማሰብ ወደ ሰላም መምጣታቸው የሚመሰገን ነው ብለዋል።
በተመሳሳይም ሌሎችም ይህንኑ አርአያ በመከተል ለውይይትና ለንግግር ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም ነው ያነሱት።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከ60 በላይ የሚሆኑ ክልላዊና ሀገራዊ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው።