ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ለምርጥ ዘር አቅርቦት ትኩረት ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ለምርጥ ዘር አቅርቦት ትኩረት ሰጥቷል
አዳማ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ትኩረት መስጠቱን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዘነበ ወልደስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ለአርሶ አደሩ አሰራጭቷል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ ለ2017/18 የምርት ዘመን መኽር ወቅት 20ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ ምርጥ ዘር ማልማቱን ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ በራሱ መሬት ከሚያባዛው በተጨማሪ በኮንትራት እርሻ ውል ባለሃብቶችና አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የዘር ብዜቱን አካሂዷል።
በምርጥ ዘር ብዜቱ ከለማው መሬት 463ሺህ 800 በላይ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አዳዲስ የቴክኖሎጂዎችና ምርጥ ዘሮችን ተደራሽ ማድረጉንም አንስተዋል።
በተለይ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለመጨመርና በሚፈለገው መልኩ ተደራሽነትን ለማሳደግ ከክልሎች ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞችና የምርምር ማእከላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አቶ ዘነበ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘርን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ሞያዊ እገዛ ማድረጉንም ተናግረዋል።
በጥራትም በመጠንም በስፋት ለማምረት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ስር ባሉት የምርምር ማእከላትና የክልል የምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዞች ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም በስንዴና በቦቆሎ ከቁሉምሳ ግብርና ምርምር እንዲሁም በበቆሎ ምርጥ ዘር ከባኮ ግብርና ምርምር ማእከል ጋር በተለይ በመነሻ ዘር ብዜት ዙሪያ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ማእከላቱ በምርጥ ዘር ማበጠሪያ ቴክኖሎጂዎች መደራጀታቸው የዘር ብዜትን በተሻለ ጥራት፣ መጠንና አይነት ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማድረስ የጎላ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረዋል።