ቀጥታ፡

በከተማው ከ12 ኪ.ሜ በላይ አስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ ነው 

ወላይታ ሶዶ ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጀመረው ከ12 ኪ.ሜ በላይ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን በፌዴራል መንገዶች አስተዳደር የሶዶ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በጽህፈት ቤቱ የወላይታ ሶዶ አስፋልት ፕሮጀክት መሃንዲስ ኢንጂነር አክሊሉ አሳሌ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከፌደራል መንግስት በተመደበ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት የአስፋልት መንገድ ግንባታ ሥራ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተካሄደ ነው፡፡


 

አንደኛው ምዕራፍ በከተማው ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅ የሚገነባ መንገድ ሲሆን ሁለተኛው ከካዎ ጦና አደባባይ እስከ አረካ መገንጠያ ድረስ እንደሚገነባና በድምሩ 12 ነጥብ 39 ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

ከከተማው አስተዳደር ጋር በመተባበር ከ11 ነጥብ 5 ኪ.ሜ በላይ የወሰን ማስከበር ሥራ መከናወኑን ያመለከቱት ኢንጂነር አክሊሉ፣ የግንባታ ሥራው በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።


 

የመንገዱን ግንባታ ሥራ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመንገድ ግንባታው ሥራ ተቋራጭ የቻይናው ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነርንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሀን ባዮሚንግ በበኩላቸው፤ ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የተለያዩ ማሽኖችና የሰው ኃይል በማስገባት እየተሰራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡


 

የግንባታ ፕሮጀክቱ አማካሪ መሃንዲስ ሳምሶን ፍቅሩ፤ የአስፋልት መንገዱ ያለምንም የጥራት ችግር እንዲጠናቀቅ ከአፈር ምርመራ ጀምሮ ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ እንዲከናወን ከተቋራጩ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ይህም በግንባታ ጥራት ጉድለት ሊባክን የሚችለውን የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንደሚታደግ ገልጸዋል፡፡

የአስፋልት መንገድ ግንባታው ለበርካታ ዓመታት ለህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ያነሱት ደግሞ አቶ ኢያሱ ቶማ የተባሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡


 

የመንገዱ ግንባታ የከተማውን እድገትና የንግድ እንቅስቃሴ ከማሳለጥ ባለፈ የትራፊክ አደጋን የሚከላከል መሆኑን ጠቅሰው ለስኬታማነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም