በኦሮሚያ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
ማያ ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዛሬ ተጀመረ።
አራተኛው ዙር የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻው የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በማያ ከተማ አስተዳደር ተጀመሯል።
በማያ ከተማ አስተዳደር ሐረማያ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ዳንዲ ቦሩ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በመገኘት ክትባቱን ያስጀመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ተስፋዬ ክበበው ፣ የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር (ዶ/ር) እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ናቸው።
ምክትል ሃላፊው ዶክተር ተስፋዬ ክበበው በወቅቱ እንዳሉት፤ በክትባት ዘመቻው በክልሉ ዕድሜያቸው እስከ አምስት ዓመት የሆናቸው 10 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚደርሱ ሕፃናት ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ዘመቻው ተደራሽ የሚሆነው በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች መሆኑንም አክለዋል።
የክትባት ዘመቻውን ለማስፈጸም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አመልክተው፤ ለዚህም በቂ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች እንዲሁም አስፈላጊው ግብዓት መሟላቱን ገልፀዋል።
ቤት ለቤት ከሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያልጨረሱ ህፃናትን የመለየትና ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ የማድረግ ስራ እንደሚከናወን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፤ ሌሎች ከጤና ጋር የተያያዙ ክስተቶችን የመለየት ተግባርም ይከናወናል ብለዋል።
የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዘመቻውን የተሳካ ለማድረግ በየደረጃው ካሉ የአመራር አካላት ጋር በመቀናጀት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ግብአቶችንና የሰው ኃይል ከማሟላት ባለፈም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥና የመቀስቀስ ሥራ መከናወኑን አክለዋል።