ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷ እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷ እያደገ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በምትሳትፍባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷ እያደገ መምጣቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ - ጆሃንስበርግ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በአፍሪካና ኢትዮጵያ ተስፋዎች እና በመደመር እሳቤ ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ በግልፅ ታይቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ወቅት ያደረጉት ንግግርና ውይይቶች የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ከፍታና ተደማጭነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ ከቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ፍሬያማ የጎንዮሽ ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤና የሁለትዮሽ ውይይቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ የአፍሪካ የጋራ ጉዳዮችን የተመለከቱ መልዕክቶች መተላለፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ያስተላለፉት ቁልፍ መልዕክት ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አጀንዳ ሰጪ መሆኗን በግልጽ አሳይቷል ብለዋል፡፡
የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከሀገር በቀል እሳቤ የተቀዳ ለአፍሪካ ሞዴል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረጓን ገልጸው፤ ከለውጡ በኋላ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራትን አንጸባርቃለች ብለዋል፡፡
የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን የሚበጅ መሆኑን በመጥቀስ፤ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት እሳቤ ለመውጣት መነሻ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡