ቀጥታ፡

ሙስናን የመከላከል ትግልን መላው ማህበረሰብና ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ሙስናን የመከላከል ትግልን መላው ማህበረሰብና ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።

22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ደረጃ ተከብሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ቀኑን ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ሊሆን ይገባል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግናችን ፀር፣ የኢፍትሀዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል ሲሉ ገልጸዋል።


 

በዚህም እንደ አገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግስትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ መዋሉ አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት መቻሉን አመልክተዋል።

መንግስታዊ / ስርአታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ብንችልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ኃላፊዎች እና ሰራተኞች የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉበኝነት ከፍተኛ ትኩረት ይሻል ነው ያሉት።

ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እና ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በማጠናከር፣ መንግስታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።


 

ቤተሰብ፣ማህበረሰቡ፣የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመሆኑም የፀረ ሙስና ትግሉን ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነም ነው ከንቲባዋ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም