የጤና አገልግሎቱን ከሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴሌ ጤና ጋር በማቀናጀት ተደራሽ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና አገልግሎቱን ከሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴሌ ጤና ጋር በማቀናጀት ተደራሽ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦የጤና አገልግሎት ከሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴሌ ጤና ቴክኖሎጂ ጋር በማቀናጀት ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሒ ገለፁ።
ጤና ሚኒስቴር "የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የቴሌ ጤና ቴክኖሎጂ ለጤናው ዘርፍ የሚኖራቸው የወደፊት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የባለድርሻ አካላት ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሒ እንደገለፁት፥ መንግስት የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር በጤናው ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል ጥራቱ የተረጋገጠ አገልግሎት እየተሰጠ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ለህክምና አገልግሎት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ላይ በመመስረት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማጠናከር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን መጠቀም ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይም በወረርሽኝ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ቅድመ ትንበያና የተቀናጀ ምላሽ አሰጣጥ ላይ አይነተኛ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።
የጤና ስርዓቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አዳዲስና ፈጠራ የታከለባቸው ቴክኖሎጂዎች በተገቢው መልኩ ተግባራዊ እየተደረጉ ስለመሆኑም አንስተዋል።
በ2016 ዓ.ም የተሻሻለው አዲሱ የጤና ፖሊሲ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በተገቢው መልኩ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚደግፍ መሆኑ ለአተገባበሩ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የጠቀሱት።
በተለይም ለጤና ምርመራ፣በታካሚዎች መረጃና የህክምና ታሪክ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ለመስጠትና በርቀት ለሚሰሩ የቴሌ ጤና አገልግሎት መጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ይህም በጤናው ዘርፍ በ2030 ለማሳካት የተቀመጠውን ግብ ከዳር ለማድረስ አይነተኛ ሚና እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታዋ አብራርተዋል።
ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘበ የጤና ስርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።