የጋራ ምክር ቤቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ምክር ቤቱ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የጋራ ምክር ቤቱ ከክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እና የክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ጋር የ2017 ሪፖርትና የ2018 ዕቅድ ማዕቀፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ፣ የክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው።
ሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት የሚሳተፉበትና ሃሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት ምህዳር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አጀንዳ አሰባስቦ ከማቅረብ ጀምሮ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛ እና ግልጽ እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስራ አስፈጻሚ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ በፓርቲዎች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር አበረታች ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።
ፓርቲዎች በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ በሰላም፣ በልማትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፣ መቻቻልን ለማጎልበትና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።