ዘላቂ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የበደሉትን ሕዝብ በልማት እንዲክሱ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች የበደሉትን ሕዝብ በልማት እንዲክሱ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ ነው
ጎንደር፤ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችን የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የበደሉትን ሕዝብ በልማት ለመካስና ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታወቀ።
ቀደም ሲልም የሰላም አማራጭን ተከትለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው እራሳቸውን እንዲችሉ ሰፊ ጥረትና ድጋፍ መደረጉም ተመልክቷል።
የክልሉ መንግስት እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ አንተነህ ታደሰ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ስምምነቱን ተከትሎ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች ሰላምን አማራጭ በማድረግ ሙሉ ትጥቃቸውን ለመንግስት በማስረከብ ተመልሰዋል።
የተመለሱትም በተሳሳተ መንገድ በሕዝቡ ላይ በደል በመፈጸማቸው በመፀፀት የሰላምን አማራጭ በመከተላቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
በወገራ፣ በኪንፋዝ በገላ፣ በአለፋ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በጭልጋና በታች አርማጭሆ ወረዳዎች የተመለሱት የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የበደሉትን ሕዝብ በልማት በመካስ ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህም ውስጥ በወገራ ወረዳ ለቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ጠቅሰው፤ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
መንግስት የሰላም አማራጭን በመከተል የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም በኩል ባለፈው ዓመት ወደ ቀደመ ስራቸው የተመለሱ እንዳሉም አውስተዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው እራሳቸውን እንዲችሉና ህይወታቸውንም እንዲመሩ መንግስት ሰፊ ጥረትና ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡ ሰላሙን ለማፅናት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል አመልክተው፤ የሰላምን አማራጭ በማይቀበሉ የሽፍታ ሰብስቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡