የባሌ ዞን አርሶአደሮች ጥራቱን የጠበቀ ቡና በመሰብሰብ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባሌ ዞን አርሶአደሮች ጥራቱን የጠበቀ ቡና በመሰብሰብ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩ ነው
ሮቤ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን ጥራቱን የጠበቀ ቡና በመሰብሰብ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰሩ መሆናቸውን በዞኑ የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በዞኑ በቡና አብቃይ ወረዳዎች ከ44 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማውን ቡና ጥራትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የለቀማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል።
በልማቱ ከተሰማሩ የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አህመድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ ለቡና ጥራት በተሰጠው ትኩረት በቡና አመራረት ሂደት ላይ በተግባር የተደገፈ ሥልጠናና የጥራት ማስጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የለቀሙትን ቀይ ቡና በድጋፍ ባገኙት የቡና ማድረቅያ ሽቦ ላይ በማድረቅ ከአምና የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቡና ልማት የመሳተፍ የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም ከምርጥ ዝርያ አጠቃቀም ምክንያት የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የገለጹት ደግሞ ሌላው የወረዳ አርሶ አደር ኡስማን ማህሙድ ናቸው።
ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ መንግሥት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጓዳኝ በአመራረት ሂደትም ቀይ ቡናን ብቻ በመልቀም ጥራት ያለው ቡና ለገበያ እንዲቀርቡ ድጋፍና ክትትል በማድረጉ በዘርፉ ያላቸው ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮቹ ካለሙት የቡና ምርት ከአንድ ሄክታር ከ9 እስከ 10 ኩንታል የቡና ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የቡናን ምርታማነት በማሳደግ ጥራት ያለው ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።
ለዚህም ከልማቱ ባልተናነሰ በቡና አሰባሰብና ክምችት የሚስተዋሉ ግድፈቶችን ለማረም ለአርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት በቡና ጥራት ላይ ተግባር ተኮር ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።
አርሶ አደሩ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅም ቀይ ቡና ብቻ እንዲለቅም፣ በሽቦ አልጋ አሊያም በሲሚንቶ በተሰራ ዐውድማ ላይ እንዲያደርቅ ግንዛቤና የቁሳቁስ ድጋፍ መሰጠቱን አንስተዋል።
በዞኑ በአሁኑ ወቅት ከ44 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማውን ቡና ጥራትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የለቀማ ሥራ በማከናወን ከ437 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
እስከ አሁን በተደረገው ጥረት ከ31 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ቡና መልቀም መቻሉን ጠቁመው ከ312 ሺህ ኩንታል የሚበልጥ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ቡና መሰብሰብ መቻሉን አስታውሰዋል።
ለቡና ምርታማነትና ጥራት በተሰጠው ትኩረት ከአንድ ሄክታር የሚመረተውን ቡና 10 ኩንታል ማድረስ መቻሉን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው÷የጥራት ደረጃውም እየተሻሻለ በመምጣቱ ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ወደ 15 ሺህ ቶን ከፍ ለማድረግ መታቀዱንም አመልክተዋል።
በባሌ ዞን ከ68 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ መሆኑም ተመልክቷል።