ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

ጂንካ ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው።

የክትባት ዘመቻው ዛሬ መሰጠት የተጀመረው በክልሉ አሪ ዞን ጂንካ ከተማ አስተዳደር ገርተጵ ቀበሌ ነው።

የክትባት ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አጉኔ አሾሌ፣ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ምንተስኖት መልካ (ዶ/ር) እና የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አጉኔ አሾሌ በዚህን ጊዜ እንደገለጹት፤ ፖሊዮ ወይም የልጅነት ልምሻ ለዘላቂ የአካል ጉዳትና ሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው።


 

የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል ክትባቱን በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸው ክትባቱ ዛሬ በዘመቻ መልክ መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

ክትባቱ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሁሉም የክልል አካባቢዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር እንደሚሰጥም ተናግረዋል ።

በዘመቻው ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ ሕጻናቱ ከዚህ ቀደም ክትባቱን ቢወስዱም ባይወስዱም በዚህ ዙር መከተብ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

ከዘመቻው ጎን ለጎን  የሥርዓተ ምግብ ጉድለት ያለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶችን እንዲሁም ቆልማማ እግር ያላቸው ሕጻናትን በመለየት ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ የፖሊዮ በሽታ ህፃናትን ለአካል ጉዳት እና ሞት የሚዳርግ በመሆኑ ወላጆች ትኩረት ሰጥተው ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ አስገንዝበዋል።


 

እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ባለፉት ዓመታት ማህበረሰቡን በማሳተፍ የተሰጠው የተቀናጀ የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በዞኑ በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አግዟል።

በዞኑ የሚካሄደው የክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም