ቀጥታ፡

በክልሉ በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

ባህርዳር ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑ ተመላከተ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢንሼቲቭ እንደሀገር በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተራቁቱ   መሬትን  መልሶ በደን  በመሸፈን  እና የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር  ውሀ ሀብትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት እያተመዘገበ ይገኛል።

ባለፉት አመታት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በትኩረት  በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የክልሉን የደን ሽፋን ወደ 18 በመቶ ማሳደግ እንደተቻለም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል። 

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በተለያየ ምክንያት የተራቆተውን መሬት በደን መልሶ ለማልበስና የአየር ንብረት ሚዛኑን ለማስተካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል።


 

ተግባሩን ለማስቀጠልም በመጪው ክረምት ለሚተከሉ‎ ችግኞች በመንግስት፣ በተቋማት፣ በማህበራትና በግል ተቋማት እንዲሁም ከ75 ሺህ በሚበልጡ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የተለያዩ ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

‎እስካሁንም በ65 ሺህ 694 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች  ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፣ ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ችግኞችን ለማዘጋጀት  የችግኝ መደቦችን በማዘጋጀት ዘር ማፍሰስ መቻሉን  ገልጸዋል።

‎ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እየተዘጋጁ ካሉት ችግኞችም  1 ነጥብ 7 ቢሊዮኑ  በተራቆቱ፣ ለደን ተከላ በሚለዩና በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በሚከናወንባቸው ተፋሰሶች እንደሚተከሉም አስረድተዋል።

‎በክልሉ ባለፈው የክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከለው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መካከል በመጀመሪያ ዙር በተካሄደ ቆጠራ 86 ነጥብ 3 በመቶው ፀድቆ በመልካም ሁኔታ ላይ  እንደሚገኝም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም