ቀጥታ፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን የንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል

ጊምቢ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ወለጋ ዞን ዘመናዊ የአሰራር ዘዴን በመከተል የንብ ማነብ ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

በማር ልማት የተሰማሩ የዞኑ አርሶ አደሮች ዘመናዊ ቀፎ በመጠቀም ንብ ማነብ ከጀመሩ ወዲህ የማር ምርታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡   

ከአርሶ አደሮቹ መካካል የጊምቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዳዊት ገመቹ በባህላዊ መንገድ ማር በሚያመርቱበት ጊዜ ተጠቃሚነታቸው እምብዛም እንደነበር ያወሳሉ።

አሁን ላይ በተደረገላቸው  የባለሙያ ድጋፍ ዘመናዊ አሰራርን በመከተል በግላቸው 21 ዘመናዊ ቀፎ ተጠቅመው ንብ ማነብ ከጀመሩ ወዲህ በዓመት ከ350 ኪሎ ግራም በላይ ማር በማምረት ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ዋቅቶላ ሰለሞን፤ ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎን በመጠቀም ማር እያመረቱ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከአንድ ባህላዊ ቀፎ ከ6 እስከ 8 ኪሎ ግራም ይገኝ የነበረው አሁን ላይ ከአንድ ዘመናዊ ቀፎ ከ25 እስከ 30 ኪሎ ግራም ምርት ማግኘታቸውን አንስተዋል።

ዘመናዊ የአሰራር ዘዴን በመጠቀም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን አንስተው ልማቱን በማስፋት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ተግተው የሚሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደር አያና ካሚሶ በበኩላቸው፤ በባህላዊ ዘዴ ማር በሚያመርቱበት ጊዜ በዓመት በአጠቃላይ ከ20 አስከ 30 ኪሎ ግራም ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ዘመናዊ ቀፎን በመጠቀም ንብ ማነብ ከጀመሩ ወዲህ ከ50 አስከ 70 ኪሎ ግራም የማር ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳት ልማትና ዝርያ ማሻሻያ ቡድን መሪ አቶ ገመቺስ ታደሰ፤ በዞኑ በምርት ዘመኑ ከ12ሺህ  ቶን በላይ ማር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል። 


 

በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ዘመናዊ የአሰራር ዘዴን እንዲከተሉ በማድረግና ዘመናዊ የንብ ቀፎን በማከፋፈል እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በማጠናከር መሰራቱን አንስተዋል።


 

በዚህም በ2018 የምርት ዘመን 116ሺህ 327 ዘመናዊ ቀፎ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁኑ  47ሺህ 387 ቀፎ መከፋፈሉን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በማር ልማቱ 15ሺህ አርሶ አደሮች መሰማራታቸውንም አቶ ገመቺስ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም