የኮደርስ ስልጠና የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን አግዟል - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ስልጠና የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን አግዟል
አዶላ ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን እንዳገዛቸው የጉጂ ዞን የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከወሰዱ የአዶላ ከተማ የመንግስት ሰራተኞች መካከል ወጣት ጉደታ ገመዳ አንዱ ነው፡፡
ስልጠናው ራስን በቴክኖሎጂ በማብቃት ለደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎትን ለመስጠት ተደማሪ አቅም እንደሚሆን ወጣት ገመዳ ተናግሯል።
ከስልጠናው የኮምፒውተር ሳይንስና የሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀትን ማግኘቱ ለስራው ስኬት እንዳገዘው ገልጿል።
የወጣት ገመዳን ሀሳብ የሚጋራው ሌላው የከተማው የመንግስት ሰራተኛ ወጣት ደስታ ሀለኬ በበኩሉ ስልጠናው እውቀትና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ተወዳዳሪነቱን እንዳሳደገው ተናግሯል።
ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዱን ገልፆ ስልጠናው የዜጎችን ብቃትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ ነው ብሏል፡፡
ይህን እድል በመጠቀም የዘመነ አሰራር ለመተግበር በእውቀትና ክህሎት ለማበልጸግ ሁሉም ሰው ስልጠናውን በመውሰድ ለሀገር ልማት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ልምዱን አካፍሏል፡፡
የዞኑ ሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤት የሰው ሀብት ልማትና ስምሪት ቡድን መሪ አቶ ቢሉ ሶርሳ፤ የመንግስት ሰራተኞችን እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ 25 ሺህ ሰራተኞች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ መታቀዱን ገልጸዋል።
ስልጠናው የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው በእስካሁኑም 23 ሺህ 456 ሰራተኞች ስልጠናውን አጠናቀው የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
ስልጠናው የመንግስት ሰራተኞችን ከቴክኖሎጂው ዓለም ጋር በማስተዋወቅ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርግ አሰራርን እንዲከተሉ ማለሙን አክለዋል፡፡
ይህም በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና መንግስታዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡