መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራሮችን አስቀርቷል - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራሮችን አስቀርቷል
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 3/2018 (ኢዜአ)፡-መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራሮችን በመቅረፍ እርካታ በተሞላበት አግባብ አገልግሎቶች እንዲቀርቡ ማስቻሉ ተገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሥራት አዳሮ እንዳሉት፤ ማዕከሉ የተንዛዛና ለብልሹ አሠራር የተጋለጠውን የተቋማት አገልግሎት ከብልሹ አሠራር በፀዳ መልኩ ለማቅረብ አስችሏል።
ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ እና ይባክን የነበረውን የሰው ኃይል፣ ጊዜ፣ ጉልበት ብሎም ሀብት ከብክነት ማዳኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ ከጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም አውስተዋል።
አገልግሎቱ የተጀመረው በዘጠኝ ተቋማት በ28 አገልግሎት መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ አገልግሎቱ ወደ 35 ማደጉን አረጋግጠዋል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜም 3 ሺህ 641 ሰዎች አገልግሎቱን በአንድ ማዕከል ማግኘታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በአምስት የዞንና የከተማ አሥተዳደሮች መሶብ የአንድ ማዕከልን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።