በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ሚሊየነር የሆነው ወጣት - ኢዜአ አማርኛ
በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ሚሊየነር የሆነው ወጣት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ ያስጀመሩት የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ኢንሼቲቭ ውጤት እያስገኘ ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል የስነ-ምግብ ስርዓት እንዲጎለብትም እንዲሁ።
መርሃ ግብሩ በውጤታማነት ተጠናክሮ ከቀጠለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ ይጠቀሳል፤ ዘርፉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ሃብት ለማፍራት እያገዘ ነው።
በዚህም ውጤታማ ከሆኑ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ወጣት ዮናስ ደባሽ ይገኝበታል።
ወጣቱ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ በመርሀ ግብሩ በንብ ማነብ የጀመረውን ስራ በማሳደግ ወደ ዶሮ እርባታና መስኖ ልማት ተሸጋግሯል።
ወጣቱ ከንብ ማነብ ስራው በዓመት እስከ 200 ኪሎ ግራም የማር ምርት ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ማሳደግ ችሏል።
የንብ ማነብ ስራውን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ለማስተሳሰርም በሰቆጣ ከተማ በሚገኘው ተራራ ላይ ጥምር ጥቅም የሚሰጡ እጽዋትን እያለማ መሆኑን ይናገራል።
አሁን ላይ ስራውን እያሳደገ በዶሮ እርባታው ዘርፍ በመሰማራትም ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ገበያ መረጋጋት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በዶሮ እርባታው ዘርፍም ሦስት ሺህ ጫጩቶችን በማሳደግ ስራ የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ስምንት ሺህ የሁለት ወር የዶሮ ጫጩቶችን በማሳደግ ለአካባቢው ገበያ እያቀረበ እንደሚገኝም አንስቷል።
በዘርፉ ለ20 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር የቻለው ወጣት ዮናስ፤ አሁን ላይ 20 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሃብት ማፍራት ችሏል።
ወጣቱ ስራውንም ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ከከተማ አስተዳደሩ አንድ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተቀብሎ እያለማ መሆኑን ገልጿል።
በወጣቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ እህትወይ መለሰ በሰጡት አስተያየት፤ የወጣቱ ጥንካሬና ታታሪነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
እሳቸውም በዶሮ ጫጩት ማሳደጊያ ማዕከሉ በተፈጠረላቸው የስራ እድል በሚያገኙት የወር ገቢ ቤተሰቦቻቸውን ከማስተዳደር አልፈው ስለዶሮ እርባታ ልምድና እውቀት ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ አያሌው፤ በአስተዳደሩ የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ኢንሼቲቭ የሕብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
መርሀ ግብሩ ከምግብ ዋስትና ባለፈ አኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግና ለስራ እድል አቅም እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንዲያስችል የብድርና የመስሪያ ቦታ ከማቅረብ ባለፈ ድጋፍና ክትትል ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ወጣቶች የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩት እያሳደጉ በማርባት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መሆኑንም ተናግረዋል።