ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ መታሰቢያ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከሲዳማ ቡና ይጫወታሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ በሊጉ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ  ሰባት ጊዜ ተሸንፏል።  በቀሪው ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በስምንት ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው  ሲዳማ ቡና እስከ አሁን በሊጉ ባካሄዳቸው 10 ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በአራቱ ተሸንፏል። በሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። አራት ግቦችን በነዚህ ጨዋታዎች ከመረብ ላይ ሲያገናኝ 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ሲዳማ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ12 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ባህር ዳር ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል  አንዱን ብቻ ያሸነፈው ባህር ዳር ከተማ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 16 ጎሎችን አስተናግዷል።

ባህር ዳር ከተማ በአራት ነጥብ የመጨረሻውን 14ተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ 11 ጨዋታዎችን አድርጎ  አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር 22 ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በአምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የዕለቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር አዲስ አዳጊዎቹ ይርጋጨፌ ቡና እና ሸገር ከተማን ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

ይርጋጨፌ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ በአራቱ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ግቦችን እሰተናግዷል። 

ቡድኑ በ10 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በሊጉ ባከናወናቸው 10 ጨዋታዎች ሰባቱን ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዷል። 

ሸገር ከተማ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ21 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም