ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአማካይ 13 ነጥብ 9 በመቶ የስኳር ይዘት ያለው የሸንኮራ አገዳ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአማካይ 13 ነጥብ 9 በመቶ የስኳር ይዘት ያለው የሸንኮራ አገዳ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 2/2018 (ኢዜአ)፡-ለወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ በአማካይ 13 ነጥብ 9 በመቶ የስኳር ይዘት ያለው የሸንኮራ አገዳ እየቀረበ መሆኑ ተገልጿል።
የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እዩኤል ለላንጎ፤ ሸንኮራ አገዳ ወደ ፋብሪካው የሚያጓጉዙ ማሽነሪዎች እና የፋብሪካው የጥገና ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ የማምረት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ፋብሪካው የስኳር ምርት እያወጣ መሆኑን ሃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
ፋብሪካው በያዝነው በጀት ዓመት ሸንኮራ አገዳ ፈጭቶ በ21 ሠዓት ከ20 ደቂቃ ውስጥ ስኳር ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም በሀገራችን የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ በአጭር ጊዜ የስኳር ምርት የተገኘበት ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል ብለዋል።
ፋብሪካው በጥራት በመጠገኑ፣ ሸንኮራ አገዳው ጥራት ያለው እና አቅርቦቱም ባልተቆራረጠ ሁኔታ በመቅረቡ የተገኘ ውጤት ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የስኳር ምርት ለማውጣት ቀደም ሲል 78 ሠዓት፣ በ2016 ዓ.ም 30 ሠዓት እንዲሁም በ2017 ዓ.ም 28 ሠዓት ይፈጅ እንደነበርም አውስተዋል።
የሸንኮራ አገዳዎችን ዝርያ የማሻሻል፣ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት፣ ስኳር የማምረት ዐቅምና የጨመቃ ሂደት ላይ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች በጥገና ወቅት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ለዘንድሮው ስኳር የማምረት ሥራ በአማካይ 13 ነጥብ 9 በመቶ የስኳር ይዘት ያለው የሸንኮራ አገዳ ለፋብሪካው እየቀረበ መሆኑንም አመላክተዋል።