ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ያለ ልዩነት መረባረብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ያለ ልዩነት መረባረብ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ በዘመናት መካከል አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ዕድል በመሆኑ ለስኬቱ ያለ ልዩነት ልንረባረብ ይገባል ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ (National Plenary) ለመጀመር የሚያስችለውን ዝግጅት እያጠናቀቀ እንደሚገኝ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተደረገው ውይይት ተገልጿል።
በውይይቱ የትግራይ ክልልን ጨምሮ አንዳንድ ቀሪ ተግባራትን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በአጭር ጊዜ ማስጀመር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክር ተደርጓል።
በትግራይ ክልል ወደ ምክክር ለመግባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተደራጀ መንገድ መከናወናቸው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ የተለያዩ የቅድመ አጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኮች መካሄዳቸውና ከመድረኮቹም ጠቃሚ ግብዓቶች መገኘታቸው ተነስቷል።
በክልሉ አጀንዳ በማሰባሰብ እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎችን በማስመረጥ ምክክሩን ምሉዕ ለማድረግ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ሥነ-ዘዴን በመጠቀም ቀሪ ሥራዎችን ማጠናቀቅ እንዲቻል በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
ለዚህም መላው የትግራይ ህዝብ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ለሚያከናውነው አጀንዳ የማሰባሰብ እና የጉባኤ ተሳታፊዎችን የማስመረጥ ሥራ የበኩላቸውን ቀና ትብብር እንዲያደርጉ መልዕክት ተላልፏል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ታሪካዊ፣ ከአንድ ትውልድ የተሻገረ፣ ከአንድ ፓርቲና ከአንድ ሥርዓት በላይ ከፍ ያለ፣ በዘመናት መካከል አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ዕድል እና ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የገለጸው ምክር ቤቱ፤ መላው ኢትዮጵያውያን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ያለልዩነት እንዲረባረቡ መልዕክት አስተላልፏል።
የሰላም በሩ ዛሬም ክፍት እንደሆነ በመግለጽም፣ ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል እና በተለያዩ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጭምር በሰላማዊ መልኩ ጥያቄያቸውን በአጀንዳነት ለምክክር ኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ በድጋሚ ጥሪ አቅርቧል።
የቆየውን ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህላችንን ከመሠረቱ ለመቀየር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወት ጥሪ በማስተላለፍ ምክር ቤቱ ውይይቱን አጠናቅቋል።
በውይይቱ ላይ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና እና ምክትልን ጨምሮ ሁሉም ኮሚሽነሮች፣ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።