ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለቀጣናዊ ትስስር እና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለቀጣናዊ ትስስር እና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) አሳሰቡ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአምባሳደሮች ኮሚቴ ስብሰባ ትናንት በጅቡቲ ተካሄዷል።


 

በስብሰባው ላይ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና የአምባሳደሮች ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።

የአምባሳደሮች ኮሚቴ የኢጋድ ከእ.አ.አ 2026 እስከ 2030 የሚቆይ ስትራቴጂ አፅድቋል።

በተጨማሪም ኮሚቴው የ2026 የኢጋድ በጀት ላይ በመምከር ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል።

የቀጣናዊ ተቋሙ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ሰላማዊ፣ የተሳሰረ እና ለፈተናዎች የማይበገር ቀጠና ለመገንባት የሀገራት የጋራ ትብብር እና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በተያያዘም የኢጋድ የአምባሳደሮች ኮሚቴ ከስብሰባው ጎን ለጎን የኢጋድ አዲሱን ዋና መስሪያ ቤት የግንባታ ሂደት ተመልክተዋል።

የመሰረተ ልማት ግንባታው ተቋማዊ አቅም እና የጋራ ትብብር ለማጠናከር እንደሚያስችል ዋና ፀሐፊው መናገራቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢጋድ የአምባሳደሮች ኮሚቴ የቀጣናዊ ተቋሙ አባል ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶችን ያቀፈ ነው።

ኢጋድን ማማከር፣ የፖሊሲ ተፈጻሚነት ክትትል እና ድጋፍ፣ የአባል ሀገራት አሰራርን የተቀናጀ ማድረግ፣ ምክረ ሀሳቦች እና የውሳኔ ሀሳቦችን ማቅረብ ወይም ማፅደቅ የኮሚቴው ዋና ተግባራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም