የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ጥንቃቄዎች... - ኢዜአ አማርኛ
የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ጥንቃቄዎች...
የጥርስ እና ተያያዥ ህመሞችን ቀድሞ እንዴት መከላከል እንደሚቻል እና በህመም ላይ ከሆኑም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች የአፍና የጥርስ ሐኪም እና መምህርት ዶክተር ካሰች አያሌው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
የጥርስ ህመም መንስዔ…
• ለጥርስና ተያያዥ ህመም አጋላጭ ምክንያቶች በርካታ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ካሰች፤ ከእነዚህ መካከል፡- የጥርስ ባክቴሪያ፣ የተመጣጠነ አመጋገብ አለመኖር (ጣፋጭ ምግቦችን ማዘውተር)፣ በትጋት የአፍ ንጽህናን አለመጠበቅ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣት፣ ጫት መቃም እና አደጋዎች ጥቂቶቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
• በተጨማሪም ጭንቀት፣ የሆርሞን ተጽዕኖ፣ የውስጥ የጤና ሁኔታ መታወክ (ለምሳሌ፡- የልብ፣ የኩላሊት፣ የላይኛው መተንፈሻ አካል እና የስኳር ህመም)፣ በዘር ሐረግ የመተላለፍ ሁኔታ፣ በቂ ፍሎራይድ ያለው የጥርስ ሳሙና አለመጠቀምና የብሩሽ ንጽህና መጓደልን ዘርዝረዋል።
የጥርስ ህመም ተጋላጭነትን ለመቀነስ…
• የአፍ እና የጥርስ ንጽህናን መጠበቅ (ከቁርስና ከእራት በኋላ በቀን ሁለት ጊዜ ከ3 እስከ 5 ደቂቃ ጥርስን መቦረሽ)፣ አመጋገብን ማስተካከል (ጣፋጭ ምግቦችን አለማዘውተር፤ ለጥርስ ጤና ጠቃሚ ምግቦችን መመገብ)፣ ቢያንስ በ6 ወር አንድ ጊዜ የአፍ ውስጥ ጤና ምርመራ ማድረግ፤ በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚጎዱ ተጓዳኝ የጤና ችግሮች ካሉ አስፈላጊውን የሕክምና ክትትል ማድረግ ለጥርስ ህመም የመጋለጥ ዕድልን እንደሚቀንሱ አስገንዝበዋል።
የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች…
• ባለሙያዋ እንዳሉት፤ የጥርስ ህመም ያለባቸው ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ያለውን የህመም ሁኔታ በምርመራ አረጋግጠው የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
• ህመሙ እንዳይባባስ የአመጋገብ ሁኔታን ማስተካከል እንዲሁም ጨው የተጨመረበት ለብ ያለ ውኃን በመጠቀም ከምግብ በኋላ አፍን መጉመጥመጥ እንደሚመከርም ገልጸዋል።
ሕክምናው…
• የጥርስና ተያያዥ ህመም ሕክምና ህመሙ እንደተከሰተበት ቦታ፣ እንደ ህመሙ ቅለትና ውስብስብነት በምርመራ ተለይቶ ከጊዜያዊ እስከ ዘላቂ ሕክምናዎች እንደሚሰጥ ዶክተር ካሰች ገልጸዋል። ሕክምናው ጥርስን ባለበት ከማከም በነቀላ እስከማስወገድ እንደሚደርስም ጠቁመዋል።