ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር ሰብዓዊ ልማት እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር ሰብዓዊ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ ገለጹ።

በአፍሪካ ቀንድ ሰብዓዊ ልማትን ለማረጋገጥ ዘላቂ ሰላምን ማስፈንና ዘላቂ የመቋቋም አቅም ግንባታ ላይ የአጋር ድርጅቶች ትብብርን ማጠናከር ዓላማ ያደረገ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

ጉባኤው በኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ኮይካ) አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን፤ በሰብዓዊ ልማትና ሰላም ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ታድመዋል።

የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ በጉባዔው ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ጠንካራ ትብብር በመፍጠር ሰብዓዊ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ነው።  

በተፈጥሮ ሀብትና አካባቢ ጥበቃ ላይ በማከናወን ላይ ያለችው ተግባር በቀጣናው የሚያጋጥመውን ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከል የሚያስችልና በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ይሁንና በቀጣናው አደጋን መቋቋም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠርና ግጭቶችን ቀድሞ የመከላከል ስራዎች መከናወን እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የሰው ሃይልና የሃብት እጥረት ለማሟላት አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው፤  የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰው፤  በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ሰብዓዊ ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትብብር ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሪያ በሰብዓዊ ልማት ላይ ያላትን የተሻለ ተሞክሮ በማካፈል በቀጣናው ልማት እንዲረጋገጥ ከሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር የድርሻዋን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም