ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ ማዕከል ለመሆን በቁርጠኝነት ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ ማዕከል ለመሆን በቁርጠኝነት ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ ማዕከል ለመሆንና ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "ለሰላም፣ ለልማት እና ለጋራ ብልጽግና አህጉራዊ አጋርነትን ማጠናከር" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት አዲስ የህዋ ፎረም ተካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን ህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ ነው።
በፍጥነት እያደገ የመጣው የህዋ ሳይንስ በአገራት ልማት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ ለሳተላይት ኮሙኒኬሽንና ለሌሎች ስራዎች ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካ በህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ ያላት ውክልና በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወን እንሰራለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከርና በስትራቴጂክ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደም ለመሆን ቁርጠኛ መሆኗንም ገልጸዋል።
ፎረሙ አዲስ አበባን በህዋ ሳይንስ ዘርፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ግዛቸው አሥራት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰላም ግንባታና የብልጽግና ስራዎችን ለማጎልበት በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
ዲፕሎማሲው በዓለም አቀፍ የህዋ ሳይንስ አስተዳደር የአፍሪካን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ትብብርን ለማጠናከር፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን ተደራሽነት ለማጠናከር እገዛ እንደሚያደርግም አብራርተዋል።
በዘርፉ ምርምርና መረጃ ልውውጥ በማድረግ የአፍሪካን የጋራ አቅምና ቀጣናዊ ትብብር ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ኢንስቲትዩቱ የእውቀት፣ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።
የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፖሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይሽሩን አለማየሁ( ዶ/ር)፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ለህዋ ሳይንስ ዲፕሎማሲ ምቹ ናት ብለዋል።
አዲስ አበባን በዘርፉ የዲፕሎማሲ ማዕከል ማድረግ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን አቅም ለማሳየት የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የጂኦ ስፓሻልና ማኔጅመንት ተጠሪ አንድሬ ኖንጉርማ እንደተናገሩት፤ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ የአፍሪካውያንን የጋራ ስራ ማጠናከር ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ውጤታማ ስራዎች እያከናወኑ ከሚገኙ አገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የመሪነት ሚና ለመወጣት የሚያስችል አቅም እንዳላት ተናግረዋል።