ቀጥታ፡

ማዕከሉ ወጣቶችን የቻይንኛ ቋንቋ ከማስተማር ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2018(ኢዜአ)፦የቻይና ቋንቋ ማዕከል ወጣቶችን የቻይንኛ ቋንቋ ከማስተማርና ክህሎታቸውን ከማዳበር ባሻገር የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን የቻይና ቋንቋ የኦንላይን ቋንቋ ክህሎት ውድድር ሽልማት በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ተካሂዷል፡፡


 

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢንስቲትዩት ሥር የተቋቋመው የቻይና ቋንቋ ማዕከል በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ልውውጥ ለማጠናከር ያስችላል፡፡

ማዕከሉ በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ ግንኙነት ለማጠናከር ገንቢ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያውያንን የቻይንኛ ቋንቋ ክህሎት ለማሳደግ በሁሉም ማህበራዊ ሚዲያዎች ተጽዕኖ የፈጠሩና ከፍተኛ ተከታይ ያፈሩ ወጣቶች እንዲወዳደሩ ተደርጎ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ብለዋል፡፡


 

ይሄውም ወጣቶች የቻይንኛ ቋንቋ ክህሎታቸውን ከማዳበር ባለፈ የትብብርና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ማወቃቸው ተወዳዳሪነታቸውን ያሳድጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቻይና ቋንቋ ማዕከሉም ቋንቋውን እንዲማሩ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡


 

የውድድሩ ዓላማም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የባህል ልውውጥ በማሳደግ የኢትዮጵያውያንን ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ያሳድጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የባህል አማካሪ ዣንግ ያዌ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 55 ዓመታትን ተሻግሯል ብለዋል፡፡


 

በእነዚህ ዓመታት የሁለቱ ሀገራት የባህል ልውውጥ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባና ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ዘመን ስልጣኔ ባለቤቶች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ የባህል ልውውጡም አስደናቂ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቻይና ቋንቋን መማር ስለ ቻይና የጠራ ግንዛቤ መያዝ ያስችላል ያሉት አማካሪዋ፤ ለሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ትብብርም ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም